ውድድሩ "የትምህርት ቤቶች ስፖርት ሊግ ውድድርን ባህል በማድረግ ጤናማ ንቁና ብቁ ትውልድ እንፈጥራለን" በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን ጋር በጋራ በመሆን የስፖርታዊ ሊግ ውድድሩ ሂደቱን በማስመልከት በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የተማሪዎችና መምህራን የስፖርት ሊግ ውድድር በትምህርት ተቋማት ባህል ሆኖ ጤናማ ንቁና ብቁ ዜጎችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት የሚያስችል መርሀ ግብር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በጋዜጣዊ መግለጫው ጠቁመው በነገው እለት በአዲስ አበባ ስቴዲየም በድምቀት በሚጀመረው 10ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና መምህራን የስፖርት ሊግ ውድድር የመክፈቻ ፕሮግራም ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮችን እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ከ30,000 በላይ ታዳሚዎች እንደሚገኙ አመላክተዋል።
ዶክተር ዘላለም አያይዘውም ስፖርታዊ ውድድሩ በተማሪዎችና መምህራን መካከል ወዳጅነትን ከማጠናከሩ ባሻገር የተማሪዎችን ስብዕና በመገንባት በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል መርሀ ግብር እንደመሆኑ ውድድሩ ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ተካሂዶ እንዲጠናቀቅ ቢሮው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው ትምህርት ቤቶች የወደፊት የሀገር ተረካቢ ዜጎች የሚፈሩባቸው ተቋማት ከመሆናቸው ባሻገር ተተኪ ምርጥ ስፖርተኞች የሚወጡባቸው ስፍራዎች መሆናቸውን ገልጸው የስፖርት ሊግ ውድድሩ እስከ ሚያዝያ 4/2017ዓ.ም ድረስ በተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደሚካሄድ በመጥቀስ ተቋማቸው ተገቢውን የቴክኒክና ሌሎች የድጋፍና ክትትል ስራዎችን እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ስፖርታዊ ውድድሩ በአትሌቲክስ፣በጠረጴዛ ቴኒስ፣በቼዝ፣በቅርጫት ኳስ፣በመረብ ኳስ ፣በእግር ኳስ፣በእጅ ኳስ፣በውሀ ዋና፣በባህል ስፖርቶች፣በገመድ ጉተታ እንዲሁም የፓራሌምፒክ የውድድር አይነቶች በተማሪዎች እና በመምህራን መካከል ከትምህርት ሰአት ውጭ እንደሚካሄድ በጋዜጣዊ መግለጫው የተጠቆመ ሲሆን በመርሀ ግብሩ ማጠቃለያ የውድድሩ አጋር በሆነው ዋናው ትጥቅ አቅራቢ ድርጅት ለውድድሩ የቀረበ ትጥቅ የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል።
.