የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ዳይሬክቶሬት አለም አቀፉን የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን"ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽን በዘላቂነት እናረጋግጥ" በሚል መሪ ቃል አጠቃላይ የቢሮው ሰራተኞች በተገኙበት አከበረ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ በመርሀግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት በሀገር አቀፍም ሆነ በከተማ ደረጃ የኤች አይ ቪ ኤድስ የስርጭት ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው የቢሮው ሰራተኞች በሚኖሩበት አከባቢም ሆነ በስራ አጋጣሚ በየትምህርት ተቋማቱ በሚያካሂዱት ድጋፍና ክትትል ቫይረሱ እያደረሰ የሚገኘው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ግንዛቤ በመፍጠር ስርጭቱን ለመከላከል የሚሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ በላይነሽ የሻው በበኩላቸው የዘንድሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን በሀገራችን ለ37ኛ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ "ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽን በዘላቂነት እናረጋግጥ" በሚል መሪ ቃል በመከበር ላይ መሆኑን ጠቁመው የቫይረሱ ስርጭት እያደረሰ ከሚገኘው አደጋ ህብረተሰቡ ራሱን እንዲከላከል ከትምህርት ቤት ጀምሮ በየደረጃው ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመርሀግብሩ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ስንታየሁ ጎሹ የግንዛቤ ምስጨበጫ ስልጠና ሰተው ውይይት ተካሂዷል።
.