Announcement የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን ትራንስፎርም ለማድረግ ለተመረጡ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የክፍል ውስጥ ግብዓቶች ስርጭት ተካሄደ::

የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን ትራንስፎርም ለማድረግ ለተመረጡ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የክፍል ውስጥ ግብዓቶች ስርጭት ተካሄደ::

03rd October, 2025

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በ2018 ትምህርት ዘመን በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ትራንስፎርም ለማድረግ ከ11 ዱ ክፍለ ከተሞች ለተመረጡ 20 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የክፍል ውስጥ ግብዓቶች ርክክብ አድርጓል::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ  ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በግብአት ስርጭቱ ወቅት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ቢሮው የቅድመ አንደኛ ትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ትራንስፎርም ለማድረግ በከተማ አስተዳደሩ የተሰጠውን ሀላፊነት ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን ተናግረው ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ የግብዓቶች ማሟላት የትምህርት ስራችንን ስኬታማ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል::

በጨዋታ የማስተማር ስነዘዴን ተግባራዊ ማድረግ ህፃናቱ አካባቢያቸውን ፤ ሳይንሳዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ጠንቅቀው እንዲያውቁ ያደርጋል ያሉት ዶክተር ዘላለም በታችኛው የትምህርት እርከን ላይ ትኩረት በመስጠት ትምህርት ቤቶችን በማዘመንና በግብዓት በማሟላት እንዲሁም ሞዴል የሆነ የትምህርት ስርዓት ለመዘርጋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል:: ትራንስፎርም ለመደረግ የተመረጡ ትምህርት ቤቶችም የክፍል ውስጥ ግብዓቶቹን ለታለመለት አላማ ብቻ በማዋል የተማሪን ስነልቦናና እድሜ ደረጃ ያገናዘበ የማስተማር ስነዘዴን በመጠቀም ብቁ ዜጋ መፍጠር እንደሚገባቸው አሳስበዋል:: 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ ወንድሙ ዑመር በበኩላቸው ቢሮው የትምህርት ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አንፃር እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ማምጣትና ምቹ የመማሪያ አካባቢን በመፍጠር ሰፊ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ተናግረው ከነዚህ ተግባራት ውስጥ መምህራንን በጨዋታ የማስተማር ስነዘዴ በስልጠና ዝግጁ በማድረግና ትምህርት ቤቶቹን በግብዓት ማደራጀት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ተናግረዋል:: አቶ ወንድሙ አያይዘውም ትራንስፎም የሚያደርጉ ትምህርት ቤቶች ግብዓቶቹን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያስችል ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት ቢሮው በቀጣይ በሚደረግ ክትትል ተግባራዊነቱን እንደሚፈትሽ አብራርተዋል::

በግብዓት ርክክብ መርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፣ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ዑመር ፣ የቢሮ አማካሪ አቶ ጥላሁን ፈቃዱ የሁሉም ክፍለ ከተሞች ቡድን መሪዎች እና የቅድመ አንደኛ ደረጃ አስተባባሪዎች እንዲሁም ርዕሰ መምህራንና ንብረት ክፍል ባለሙያዎች ተገኝተዋል::

.

Copyright © All rights reserved.