ስልጠናው ለልዩ ፍላጎት መምህራን፣ለተዘዋዋሪ መምህራን እንዲሁም ለክፍለ ከተማ የልዩ ፍላጎት ቡድን መሪዎች እና ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን የስልጠናው ተሳታፊዎች በጋራ እና በቡድን በመሆን በቀረበው የስልጠና ማኑዋል ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገመቺስ ፍቃዱ ቢሮው ከፍተኛ በጀት መድቦ በ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ 124 የልዩ ፍላጎት ትምህርት የድጋፍ መስጫ ማዕከላት የተለያዩ ግብአቶች ማሰራጨቱን ገልጸው የዛሬው ስልጠና በድጋፍ መስጫ ማዕከላቱ የሚገኙ ግብአቶች ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ተማሪዎች ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።ዳይሬክተሩ አያይዘው በየትምህርት ቤቱ የሚገኙ የልዩ ፍላጎት ትምህርት መምህራንም ሆኑ ተዘዋዋሪ መምህራን የድጋፍ መስጫ ማዕከላቱ በሚገኙባቸው ተቋማትም ሆነ በአቅራቢያ ባሉ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የሜንቶሶሪ ግብአቶቹ አገልግሎት እንዲሰጡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። በመርሀግብሩ የቢሮ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ባለሙያ አቶ ፀጋዬ ሁንዴ የሜንቶሶሪ ግብአቶች አይነትና አጠቃቀምን መሰረት አድርጎ በተዘጋጀ ማኑዋል ዙሪያ ስልጠና ሰተዋል።
.