ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ተግባራት የተሻለ ስራ በሰሩ የትምህርት ተቋማት ልምድ ልውውጥ ተካሄደ።
(ግንቦት 28/2017 ዓ.ም) የልምድ ልውውጡ በአጼ ነአኩቶ ለአብ 1ኛ ደረጃ እና በእንጦጦ አምባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተካሄደ ሲሆን በመርሀ ግብሩ በክፍለ ከተማው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ዋና ርዕሳነ መምህራን እና የስርአተ ጾታ ክበብ ተጠሪዎችን ጨምሮ የክፍለ ከተማው እና የቢሮው የዘርፈ ብዙ ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ኮራ በክፍለ ከተማው በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በተለይም በስርአተ ጾታ ክበባት በሚከናወኑ ተግባራት የተሻለ አፈጻጸም ካላቸው ተቋማት መካከል የአጼ ነአኩቶ ለአብ 1ኛ ደረጃ እና እንጦጦ አምባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸው ተቋማቱ በስርአተ ጾታ ክበባት ማቋቋሚያ መመሪያ በተቀመጠው መሰረት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የተወጡበት መንገድ ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን በመሆኑ የልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎች ያገኙትን ተሞክሮ መሰረት በማድረግ በተቋማቸው ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙ ጉዳዮችና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ በላይነሽ የሻው በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት በክበባቱ አማካይነት በትምህርት ቤቶች አከባቢ የሚስተዋሉ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት ከወጣውን መመሪያ ጋር በተገናኘ የተሰጣቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ትምህርት ቤቶቻቸው ለሴት ተማሪዎች ምቹ የመማሪያ ቦታ እንዲሆኑ ያከናወኗቸው ተግባራት ልምድ የሚወሰድባቸው በመሆኑ የዛሬው የልምድ ልውውጥ መርሀግብር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ቢሮው ቀደም ሲል በትምህርት ቤቶች አከባቢ የሚከሰትን ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም ከህይወት ክህሎት ጋር በተገናኘ የወሰዱትን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ተግባራዊ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ቡድን መሪ አቶ ይልማ ተሾመ ጠቁመው በቀጣይ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የጾታ እክኩልነትን አረጋግጠው የሴት ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎና ውጤት ማሻሻል እንዲችሉ ስራ ክፍሉ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል።