Announcement በዓለም ዕውቅና ያገኘው የኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ምገባ ስኬት

በዓለም ዕውቅና ያገኘው የኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ምገባ ስኬት

03rd April, 2026

ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ ካከናወነቻቸው ሰው ተኮር ማኅበራዊ ልማቶች መካከል፣ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር የዜጎችን ሕይወት የቀየረና የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን በአካልና በአዕምሮ ለመገንባት የተጣለ ጠንካራ መሠረት ሆኖ ተመዝግቧል።

መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ከፍተኛ በጀት በመመደብ በወሰደው ቁርጠኛ አቋም፣ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገራችን በሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከ 9 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። 

በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልዩ ትኩረት የተጀመረውና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ የሚመግበው ተሞክሮ፣ አሁን ላይ ወደ ሁሉም ክልሎች በመስፋፋት ሀገር አቀፍ ንቅናቄ መፍጠር ችሏል።

ይህ መርሃ ግብር ከትምህርታዊ ፋይዳው ባለፈ፣ ወላጆች ያለባቸውን የኑሮ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ያቀለለ ሲሆን፣ በመዲናዋና በክልሎች በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡት ዘመናዊ የተቀናጁ የምገባ ማዕከላት ኢትዮጵያ ለሰው ተኮር ልማት የሰጠችውን ትልቅ ቦታ ማሳያ ናቸው። 

ፕሮግራሙ ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ በማስቻልና መጠነ ማቋረጥን በመቅረፍ ረገድ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የኢትዮጵያን የትምህርት ቤት ምገባ አፈጻጸም እንደ ትልቅ ተሞክሮ በመውሰድ፣ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ምገባ ለአፍሪካ ምሳሌ እንደሚሆን ጠቅሷል። 

ይህም የተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ፣ ትውልድን በዕውቀት ብቻ ሳይሆን በተሟላ ጤና እና ሥነ-ልቦና ለመቅረጽ የቻለ ያለፉት ስምንት ዓመታት ስኬታማ ድሎች ማሳያ ነው።


.

Copyright © All rights reserved.