በከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት የነገዋን ኢትዮጵያን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት መሰረት በመጣል ላይ ይገኛሉ፡፡
ደረጃቸውን የጠበቁና በአጭር ጊዜ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የመማሪያ ህንፃዎች ተማሪዎች ምቹ በሆነ አካባቢ እውቀትን እንዲቀስሙ ከማድረጋቸውም በላይ በትምህርት ጥራት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ትልቅ አቅም ሆነዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት የእውቀት ማዕከል ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ ህፃን የትምህርት ጥራት የማግኘት ሰብአዊ መብቱ በተግባር የተረጋገጠባቸው ማሳያዎችም ጭምር ናቸው።
ከለውጡ ወዲህ በትምህርት ዘርፍ የተከናወኑት ግዙፍ ስራዎች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከፍ ያደረጉና የትምህርት መሰረተ ልማት ግንባታ ፍጥነት እንዲሁም ጥራት በአስደናቂ ሁኔታ የታየበት ሲሆን ይህም በተለይ ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በተያዘው ግብ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው ነው።
በሌላ በኩል የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦትን ስንመለከት እንደ ደብተር ፣ ዩኒፎርም እና መፅሐፍት በነፃ ለተማሪዎች መቅረቡ ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ብቻ ሳይሆን ለትምህርት ፍትሃዊነትም ትልቅ ትርጉም አለው።
ይህም ኢኮኖሚያዊ አቅም ካላቸውና ከሌላቸው ቤተሰቦች የሚመጡ ተማሪዎች በእኩልነት ስሜት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመጡ አስችሏል። በትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለውን የማህበራዊ ልዩነት በማጥበብም ተማሪዎች ትኩረታቸውን በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያደርጉ የላቀ መነሳሳትን ፈጥሯል።
የተማሪዎች ምገባ መርሃ-ግብር መጀመር ለወላጆች በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች፣ ትልቅ የኢኮኖሚና የስነ-ልቦና እፎይታን ሰጥቷል። በአንድ በኩል ተማሪዎች በረሃብ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩና በአካልም ሆነ በአእምሮ በልፅገው እንዲማሩ ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆች የልጆቻቸውን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት የሚቸገሩበትን ጫና በመቀነስ የቤተሰብን ኑሮ በከፍተኛ ሁኔታ ደግፏል። ይህ ሰብአዊ ተግባር መንግስት ለዜጎቹ ያለውን አጋርነት በተግባር ያሳየበት ደማቅ ስራ ነው።
በአጠቃላይ እነዚህ የተቀናጁ ጥረቶች የነገዋን አገር ተረካቢ ትውልድ በዕውቀት፣ በጤና እና በስነ-ምግባር ለማነፅ የተሰጡ ልዩ ትኩረቶች ናቸው። ለትውልድ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ከማንኛውም ቁሳዊ ሀብት በላይ ዘላቂ በመሆኑ ዛሬ የተዘሩት የጥራትና የፍትሃዊነት ዘሮች ነገ አገሪቱን የሚመሩ ብቁ በራሳቸው የሚተማመኑና ለአገራቸው የሚቆረቆሩ ዜጎችን እንደሚያፈሩ ጥርጥር የለውም። ይህ ለትውልድ የተሰጠ ትኩረት የኢትዮጵያን የነገ ብሩህ ተስፋ ዛሬ ላይ የሚያበስር ታላቅ ስኬት ነው።
.