ፕሮጀክቶቹ በብሔራዊ እና ወርሃ የካቲት ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የG+2 የመማሪያ ህንጻዎችን እንዲሁም በምስራቅ ጎህ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የG+2 ሁለ ገብ አገልግሎት የሚሰጥ ህንጻን ያካተቱ ሲሆን የግንባታ ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ እንዲሁም የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ምስክር ነጋሽ እና የትምህርት ቢሮ አማካሪ አቶ ጥላሁን ፍቃዱን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በብሔራዊ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በመርሀግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት በከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ዘርፉ በተሰጠ ትኩረት በርካታ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ተማሪዎች ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ማግኘት ከመቻላቸው ባሻገር የትምህርት ቤቶች ደረጃ በመሻሻል ላይ መሆኑን ጠቁመው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የመማር ማስተማር ስራው ውጤታማ እንዲሆን በሶስቱ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች እና ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጡ ህንጻዎች ግንባታ በማስጀመሩ ምስጋና አቅርበው ፕሮጀክቶቹ ጥራታቸው ተጠብቆ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ሁሉም ባለድርሻ አካል ተገቢውን ክትትል እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ምስክር ነጋሽ በበኩላቸው ክፍለ ከተማው በትውልድ ግንባታ ላይ እየሰራ የሚገኘው ስራ ውጤታማ እንዲሆን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እያደረገ ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው በዛሬው እለት በሶስቱ ትምህርት ቤቶች የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የክፍለ ከተማው አስተዳደር የሚጠበቅበትን ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በትምህርት ቤቶቹ የሚገነቡት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ከክፍለ ከተማው ዲዛይንና ግንባታ ጽህፈት ቤት ጋር በጋራ እንደሚሰራ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰማኸኝ አስረስ አስታውቀዋል።
.