የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ትምህርት ሱፐርቪዥን ዳይሬክቶሬት በፈለገ ዮርዳኖስ ሱፐር ቪዥን ክላስተር ማእከል ልምድ ልውውጥ አካሂዷል፡፡
በልምድ ልውውጡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከማል ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በመልእክታቸው ላይ ልምድ ልውውጡ ተቋማት በሀሳብና በሀብት እንዲደጋገፉ በማድረግ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚያስችል ተናግረው ፤ የተቀናጀ የአሰራር ስልት በመከተል ተቋማት ወደተቀራራቢ የስራ አፈጻጸም እንዲመጡ ልምድ ልውውጥ ማካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አክለውም ፈለገዮርዳኖስ ክላስተር ማዕከል ስር ያሉ ትምህርት ቤቶች በ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከ90% በላይ እንዲሁም በተማሪ ስነምግባር የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ መሆኑን አንስተው የልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎች የሚወስዱትን ተሞክሮ በተግባር ላይ በማዋል ራሳቸውን ለተሻለ ውጤት እንዲያዘጋጁ የክላስተር ማዕከሉ ተሞክሮ የበለጠ አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የምንማረው ልንማር በፈለግነው ልክ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ከልምድ ልውውጡ የምናገኘውን ተሞክሮ ክላስተር ማዕከላት እና ትምህርት ቤታችንን ለመለወጥ የሚያስችል አቅም እንዳለው በመውሰድ ልምድ ልውውጡን ከነቃ ተሳትፎ ጋር እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰማኅኝ አስታጥቄ በበኩላቸው ትምህርት ቤቶች ሀገር ተረከቢና ትውልድን የሚገነቡ ተቋማት በመሆናቸው ወጥነት ባለውና ውጤታማ በሆነ መልኩ ራሳቸውን ለትውልድ ግንባታ ስራ ሊያዘጋጁ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ አቶ ሰማኀኝ አክለዉም ትምህርት ቢሮ በከተማ አስተዳደሩ ካሉ ተቋማት ግንባር ቀደም የሆነ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመው የሱፐርቪዥን ክላስተር ማእከላትም ይህ ውጤት የበለጠ ተጠናከሮ እንዲቀጥል ሃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ የልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎችም ከከላስተር ማእከሉ የሚያገኙትን ልምድ ወደራሳቸው በመውሰድ በተሰናሰለ መልኩ ስራን መስራትና ውጤታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
የክላስተር ማእከሉ አስተባባሪ አቶ ኃይለሚካኤል አመሃ ምርጥ ተሞክውን የያዘ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል ፡፡ በተያያዘም ተሳታፊዎች በትምህርት ቤቱ የሚገኙ የሂሳብና እንግሊዝኛ ላብራቶሪዎች ፣ የልዩ ፍላጎት ማስተማሪያ ክፍሎችና መሰል በትምህርት ቤቱ የሚገኙ ሰነዶች ላይ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡
በልምድ ልውውጡ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከማል ፣ የቂርቆስ ክፍለከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰማኅኝ አስታጥቄ ፣ የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አጠቃላይ ትምህርት ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ጥላዬ ዘውዴ ፣ የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም የሁሉም ክላስተር አስተባባሪዎች እና የፈለገዮርዳኖስ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡