Announcement የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን በየትምህርት ተቋማቱ የሚገኙ የምገባ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው ተጠቆመ።

የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን በየትምህርት ተቋማቱ የሚገኙ የምገባ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው ተጠቆመ።

23rd August, 2025

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በየትምህርት ተቋማቱ ከሚገኙ የምገባ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ጋር በትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት እና ከአገልግሎቱ ጋር በተገናኘ በተካሄደ ድጋፍና ክትትል ግብረመልስ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ ሳምሶን መለሰ በመርሀግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት በከፍተኛ በጀት ተግባራዊ ያደረገው የተማሪዎች ምገባ አገልግሎት የተማሪዎች ውጤት እና ስነምግባር እንዲሻሻል ከማድረጉ ባሻገር ለወላጆች እፎይታ መፍጠር ያስቻለ ፕሮግራም መሆኑን ገልጸዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም በየትምህርት ቤቱ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን አገልግሎቱን የሚከታተሉ የምገባ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች እንዲመደቡ መደረጉን ገልጸው ባለሙያዎቹ በ2017ዓ.ም የነበሩ አፈጻጸሞችን መሰረት በማድረግ በ2018ዓ.ም የተሻለ ስራ ለመስራት ከወዲሁ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ የሚገባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የትምህርት ግብአት ፍላጎት አቅርቦትና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ምስራቅ ብርሀነመስቀል በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ በቅድመ አንደኛ፣አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ 840,585 ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ የምገባ አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ግልጸው የምገባ አገልግሎቱ በ560 ማህበራት ለተደራጁ 12,943 መጋቢ እናቶች የስራ እድል መፍጠሩን በመጥቀስ ቢሮው በየትምህርት ቤቱ በመገኘት የምገባ አገልግሎቱን አተገባበር በድጋፍና ክትትል በማረጋገጥ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመርሀግብሩ የቢሮው የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ቡድን መሪ አቶ ናትናኤል ገብረዋድ በየትምህርት ቤቱ ያለውን የምገባ አገልግሎት መሰረት አድርጎ የተካሄደ የድጋፍና ክትትል ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።


.

Copyright © All rights reserved.