ጽህፈት ቤቱ "በሳይንስና ፈጠራ የተካነ ትውልድ ለተምሳሌታዊ ሀገር" በሚል መሪ ቃል የ2018 ዓ.ም የሳይንስና የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ማካሄድ ጀምራል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራአስፈጻሚ ዶክተር ምስክር ነጋሽ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት መሰረት ከመሆኑ ባሻገር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው የትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስራዎችን መፍጠር የሚችሉ ተማሪዎችን ማፍራት እንዲችሉ የክፍለ ከተማው አስተዳደር ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን በመግለጽ በአውደ ርዕዩ የቀረቡ የፈጠራ ስራዎች ወደ ተግባር ተቀይረው ለሚፈለገው አላማ እንዲውሉ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አማካሪ አቶ ጥላሁን ፍቃዱ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ በፈጠራ የተካነ ትውልድ ለሀገር ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ለሳይንስና የፈጠራ ስራ ትኩረት አድርጎ በመስራት ላይ መሆኑን አስታውሰው አውደ ርዕዩ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት በተግባር ቀይረው ስራዎቻቸውን ለተመልካች የሚያሳዩበትን እድል የሚያመቻች በመሆኑ ቢሮው ለዘርፉ ትኩረት አድርጎ መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
አውደ ርዕዩ በትምህርት ቤትና ወረዳ ደረጃ ተካሂዶ አሸናፊ የሆኑ ስራዎች በክፍለ ከተማ ደረጃ መቅረባቸውን እና 1,131 የፈጠራ ባለቤት ተማሪዎችና መምህራን የፈጠራ ስራዎቻቸውን ለተመልካች ማቅረባቸውን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰማኽኝ አስታጥቄ ገልጸው የፈጠራ ስራዎቹ ወደ ተግባር ተቀይረው ለሚፈለገው አላማ እንዲውሉ ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ የሚሰራ መሆኑን አመላክተዋል።