በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችለንን የዲጂታል ክህሎት ለመገብየት እየተጉ መሆኑን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ።
የአምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ የስልጠና መርኃ ግብር የዲጂታል ክህሎት ማሳደጊያ ፕሮጀክት ነው። ይህም የቴክኖሎጂ እውቀትን በማበልጸግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን ብቃት እንዳስጨበጣቸው መርኃ ግብሩን ተከታትለው የጨረሱ ሰልጣኞች በተደጋጋሚ ገልጸዋል። መርኃ ግብሩ ዜጎች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዳታ ሳይንስ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግና በዌብ ፕሮግራሚንግ ወሳኝ እውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። መንግሥት ያመቻቸውን ዕድል በመጠቀም ስልጠናውን እየወሰዱ ካሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ተማሪዎች ተጠቃሽ ናቸው።
በኮከበ ፅባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ አቤኔዘር ዘገዬወርቅ ስልጠናው ከመደበኛ ትምህርታችን ጎን ለጎን የዲጂታል አቅማችንን እንድናጎለብት አስችሎናል ብሏል። ከቀረቡት መርኃ ግብሮች መካከል በዌብ ፕሮግራሚንግ እና ዳታ ሳይንስ ስልጠና መውሰዱን ገልጿል። ያገኘው ስልጠና ጊዜው የሚጠይቀውን የዲጂታል እውቀት እንዲገበይ እንዳደረገው በመግለጽ ቀሪዎቹን የኮደርስ የስልጠና መርኃ ግብሮች በቀጣይ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ጠቅሷል።በስልጠናው በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተሻለ ክህሎት ማግኘቷን የገለጸችው ደግሞ የብርሃን ጉዞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ህይወት ተስፋሁን ናት። አርቴፌሻል ኢንተለጀንስ በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራት ትፈልግ እንደነበረ በመጠቆም መርኃ ግብሩ ፍላጎቷን እውን እንድታደርግ እንዳስቻላት ገልጻለች። በኮከበ ጽባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ሀናን ኢብራሂም በበኩሏ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስልጠና መውሰዷ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በቀላሉ መረዳት እንዳስቻላት ጠቅሳለች።
የብርሃን ጉዞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ኪሩቤል ሀብተስላሴ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በሚገባ ለመረዳት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሶ ስልጠናው ክህሎቱን ማጎልበት እንዳስቻለው ኢዜአ ገልፃል ።የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዲናኦል ጫላ ቢሮው ተማሪዎች የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ከ2017 የትምህር ዘመን ጀምሮ ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎች የኮደርስ ስልጠና መውሰዳቸውን በማስታወስ። ቢሮው የዲጂታል እውቀትና ክህሎት የተላበሰ ትውልድ ለመፍጠር የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።