ትምህርት ቤቱ በ2017ዓ.ም የትምህርት አመት ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ የእቴጌ መነን የልጃገረዶች እና ከብርሀን የአይነስውራን አዳሪ ትምህርት ርዕሳነ መምህራንና የማኔጅመንት አባላት በትምህርት ቤቱ ተገኝተው የልምድ ልውውጥ መርሀግብር አካሂደዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ እንዳለ ቢሮው በየሩብ አመቱ የትምህርት ተቋማትን የመሪ እቅድ እና የሪፎርም ስራዎችን መሰረት አድርጎ በሚያካሂደው ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ምዘና ገላን የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት አፈጻጸማቸው ከፍተኛ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ በመሆኑ ልምድ ልውውጡን ማካሄድ ማስፈለጉን ገልጸው መርሀግብሩ በዋናነት አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ ተቀራራቢ አፈጻጸም አስመዝግበው ውጤታማ መሆን እንዲችለ የሚያግዝ መሆኑን አስታውቀዋል።
ጽህፈት ቤት ኃላፊው አያይዘውም የልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎች በትምህርት ቤቱ ያገኙትን ተሞክሮ በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ የተማሪዎቻቸውን ውጤትና ስነ ምግባር ማሻሻል የሚጠበቅባቸው መሆኑን ጠቁመው ቢሮው አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።
የገላን የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ካሳሁን መርጋ ተቋሙ ወላጆችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትን አስተባብሮ በመስራቱ በተማሪዎች ውጤት ላይ ተጨባጭ መሻሻል መታየቱን በተለይም የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል የተፈተኑ ተማሪዎች በሙሉ ማለፋቸውን ገልጸው ትምህርት ቤቱ ውጤታማ እንዲሆን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በየወቅቱ የሚያደርገው የቅርብ ድጋፍና ክትትል ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም አመላክተዋል።
የልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎች በትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ልምድ የሚወሰድባቸው በመሆናቸው የተመለከቱን ተግባር በተቋማቸው ተግባራዊ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።