በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ስትራቴጂክ ካውንስል አባላትን ጨምሮ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የስራ ኃላፊዎች ፣ የመሬት አስተዳደር ቢሮ እና የህብረት ስራ ኮሚሽን አመራሮች እንዲሁም የመምህራን ማህበር ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ የቴክኒክ ኮሚቴው የመምህራንን አቅም እና ወቅታዊ ዋጋን ታሳቢ በማድረግ ባቀረባቸው የዲዛይን አማራጮች ዙሪያ በማህበር ለተደራጁ መምህራን ግንዛቤ በመፍጠር በቀጣይ በፍጥነት ወደ ግንባታ እንዲገቡ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቁመው በመሬት ልማት አስትዳደር ቢሮ በኩል ለግንባታው የሚሆን ቦታ ዝግጁ የማድረግ እና ተያያዥ ጉዳዮችን መስራት የሚጠበቅ መሆኑን አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ በበኩላችው የቴክኒክ ኮሚቴው ያቀረባቸው አማራጮች የመምህራኑን አቅም ታሳቢ ያደረጉ እና በፍጥነት ወደግንባታ የሚያስገቡ በመሆናቸው በፍጥነት ወደ ግንባታ በመግባት መምህራኑ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ተቋማቸው በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ለግንባታ የተለዩ ቦታዎችን በፍጥነት ርክክብ በማድረግ በቀረቡት የዲዛይን አማራጮች መሰረት ወደ ግንባታ መግባት እንዲቻል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የቴክኒክ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት አስታውቋል።
.