(መስከረም 5/2019 ዓ.ም) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ በዛሬው እለት በድምቀት ተጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ሳምሶን መለሰ ከአዲስ አበባ ከተማ ምገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጸዳለች ሚካኤል እንዲሁም ከለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ኃላፊ ሲሳይ ኬኔ እና ከክፍለ ከተማው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሌሊስቱ ተስፋዬ ጋር በመሆን በአባዶ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የ2019 ዓ.ም ትምህርትን በማስጀመር ተማሪዎችን አበረታተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ሳምሶን መለሰ በከተማ አስተዳደሩ ከ1.3 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች በ2019 ዓ.ም ትምህርታቸውን ለመከታተል መመዝገባቸውን አስታውሰው ቢሮው በአዲሱ የትምህርት አመት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተማሪዎችን ውጤትና እና ሥነ ምግባር ለማላቅ በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራቱን አመላክተዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም በትምህርት ዘመኑ ለተማሪዎች በቂ ደንብልብሶችን ጨምሮ ደብተሮችና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶች ዝግጁ ከመደረጋቸው ባሻገር የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ጥራቱን ጠብቆ ለተማሪዎች ተደራሽ እንዲሆን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው የትምህርት አመቱ ፍጹም ሰላማዊና ተማሪዎች ውጤታማ የሚሆኑበት አመት እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካል ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሌሊስቱ ተስፋዬ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ለማሻሻል በተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸዉን ጠቁመው ውጤቱ በ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከአምናው የተሻለ እንዲሆን ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት ፈጥሮ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የ2019 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች የምገባ መርሀ ግብርም በይፋ ተጀምራል፡፡


.