የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ከምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ሳምሶን መለሰ እና ከአዲስ አበባ ከተማ የግዢ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አመራሮች ጋር በመሆን የተማሪዎች ደንብ ልብስ አምርተው በማሰራጨት ላይ ከሚገኙ አምራች ድርጅቶች መካከል ኤልቴክስ ጋርመንት ማምረቻ እና ሌጀንድ ኢንዱስትሪ ተገኝተው ሂደቱን ተመልክተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ ትኩረት በመስጠት እና ከፍተኛ በጀት በመመደብ የተማሪዎች ደንብ ልብስን ጨምሮ የመማሪያ ደብተር፣መጽሐፍ እንዲሁም ለቅድመ አንደኛ ፣አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ጠቁመው የግብአት አቅርቦቱ የተማሪዎች ውጤት እና ስነምግባር እንዲሻሻል እያበረከተ የሚገኘው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኃላፊው አያይዘውም ቢሮው የ2018 ዓ.ም ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የተማሪዎች ደንብ ልብስ ዝግጁ እንዲሆን የ90 ቀን እቅድ አዘጋጅቶ በትኩረት በመስራቱ የደንብ ልብሶቹ ወደ ትምህርት ቤቶች በመሰራጨት ላይ እንደሚገኙ በዛሬው ምልከታ ማረጋገጣቸውን ገልጸው የደንብ ልብስ ለማቅረብ ውል የገቡ አምራች ድርጅቶች በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ መሰረት በጥቂት ቀናት ውስጥ ቀሪ ስራዎችን አጠናቀው የደንብ ልብሶቹን ለትምህርት ተቋማት ተደራሽ እንዲያደርጉ አቅጣጫ መቀመጡንም አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የግዢ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራአስኪያጅ አቶ መንግስቱ አጥናፉ በበኩላቸው ለ2018 ዓ.ም የትምህርት አመት የተማሪዎች ደንብ ልብስ ለማቅረብ ከተወዳደሩ 50 ድርጅቶች መካከል 21 አምራቾች ጨረታውን አሸንፈው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰው ኤጀንሲው ድርጅቶቹ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ መሰረት ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማቅረብ ላይ መሆናቸውን እየተከታተለ የሚገኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
.