Home የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች ስፖርት ሊግ ውድድር በትምህርት ቤት ደረጃ በድምቀት ተጀመረ።

የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች ስፖርት ሊግ ውድድር በትምህርት ቤት ደረጃ በድምቀት ተጀመረ።

15th November, 2025

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ስትራቴጂክ ካውንስል አባላት ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ እና ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በርኬ ጋር በመሆን የተማሪዎች ስፖርት ሊግ ውድድርን እንጦጦ አምባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው ውድድሩን አስጀምረዋል።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ አሊ ከማል በትምህርት ቤት ደረጃ የሚካሄድ የተማሪዎች ስፖርት ሊግ ውድድር ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባሻገር በአካል እና አዕምሮ የዳበረ ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችል መርሀግብር መሆኑን ገልጸው ውድድሩ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ተማሪዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ ዲናኦል ጫላ በበኩላቸው የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች ስፖርት ሊግ ውድድር ከትምህርት ቤት ጀምሮ በወረዳ ፣ በክፍለ ከተማ እና በከተማ ደረጃ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው ውድድሩ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ቢሮው በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል። በተጨማሪም በስነ ምግባር የታነፀ እና ጤናው የተጠበቀ ትውልድ ለማፍራት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች ስፖርት ሊግ ውድድር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮና ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በጋራ የሚያካሂዱት ስፖርታዊ ውድድር መሆኑን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ ገልጸው ለውጤታማነቱ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ አክለዉም ከትምህርት ባለፈ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የተማሪዎች ጤና እንዲጠበቅ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡በእንጦጦ አምባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በድምቀት በተጀመረው የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች ስፖርት ሊግ ውድድር መክፈቻ መርሀግብር በትምህርት ቤቱ የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ወንድ ተማሪዎች መካከል የእግር ኳስ ጫወታ ተካሂዷል።

.

Copyright © All rights reserved.