ውቅናው በቢሮ ከሚገኙ ስራ ክፍሎች ጀምሮ በክፍለ ከተማና ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም በሁሉም የመንግስት 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በሱፐርቪዥን ክላስተር ማዕከላት በተካሄደ የግማሽ አመት ምዘና የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት የትምህርት ሴክተሩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነው የተሰጠው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በዕቅና መርሀግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት ፈጥሮ ባከናወናቸው የተለያዩ ተግባራት በከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ልማት ስራው ውጤት በማስመዝገብ ላይ መሆኑን ጠቁመው የትምህርት ተቋማት ባቀዱት ዕቅድ መነሻ ያከናወኑት ተግባር ምንደረጃ ላይ እንደሚገኝም ሆነ ምን ውጤት እንዳስመዘገቡ ለማረጋገጥ የሚካሄድ ምዘና የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት ዕውቅና ከመስጠት ባሻገር ሌሎች ልምድ ቀስመው ተቋማቸውን ወደ ተሻለ የአፈጻጸም ደረጃ ማሸጋገር እንዲችሉ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኃላፊው አያይዘውም በ2018 ዓ.ም ግማሽ አመት በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ምዘና ከመካሄዱ ባሻገር ተደጋጋሚ የድጋፍና ክትትል ስራ መሰራቱን አስታውሰው በ2018 ዓ.ም ግማሽ አመት የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግበው ዕውቅና ላገኙ ተቋማት እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ሌሎች ተቋማት በቀጣይ የተሻለ ስራ በመስራት ለዕውቅና እንዲበቁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ አማካሪና የዘርፉ አስተባባሪ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በበኩላቸው በትምህርት ተቋማት የሚካሄድ ምዘና ተቋማቱ ተቀራራቢ አፈጻጸም አስመዝግበው የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር እንዲሻሻል የሚያስችል ተግባር መሆኑን ገልጸው በ2018 ዓ.ም ግማሽ አመት በ614 ተቋማት ምዘና ተካሂዶ ለዛሬው የዕውቅና መርሀግብር መብቃቱን አስታውቀዋል።
በመርሀግብሩ የ2018 ዓ.ም ግማሽ አመት አፈጻጸም ሪፖርት በእቅድና በጀት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ለማ ከመቅረቡ ባሻገር የተቋማት የቁልፍና አበይት ተግባራት ምዘና ሪፖርት በሪፎርም ዳይሬክተር አቶ ፈንታሁን እያዩ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።