Home የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች የስፖርት ሊግ እና የመምህራን ውድድርን በድምቀት አስጀመረ።

የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች የስፖርት ሊግ እና የመምህራን ውድድርን በድምቀት አስጀመረ።

27th December, 2025

 "በአካሉ ብቁና በአዕምሮው ንቁ ትውልድ ለሀገር ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል በቦሌ ህብረተሰብ ትምህርት ቤት በድምቀት በተጀመረው ክፍለ ከተማ አቀፍ ውድድር በክፍለከተማው ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች፣መምህራን፣ርዕሳነ መምህራን ፣ወላጆች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የትምህርትና ስፖርት ሴክተር አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የመክፈቻ መርሀግብሩ የክብር እንግዳ አቶ አሊ ከማል በትምህርት ቤቶች የሚካሄድ ስፖርታዊ ውድድር  በእውቀቱ የነቃ እና በአካሉ የበቃ ትውልድ በመፍጠር ለመማር ማስተማር ስራው ውጤታማነት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው የቦሌ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ውድድሩ በድምቀት እንዲጀመር ላከናወነው ተግባር ምስጋና በማቅረብ ተወዳዳሪዎች ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ውድድሩን እንዲያካሂዱ ጥሪ አቅርበዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ታደሰ በበኩላቸው የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች የስፖርት ሊግ እና የመምህራን ውድድር ቀደም ሲል በትምህርት ቤት ደረጃ ሲካሄድ መቆየቱን ጠቁመው ውድድሩ ሁለንተናዊ ስብዕናው የተገነባ ትውልድ ከመፍጠር ባሻገር ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችል በመሆኑ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

ውድድሩ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት የሚጠበቅበትን ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አንዱአለም አሰፋ አስታውቀዋል።

በመክፈቻ መርሀ ግብሩ በአየር አምባ እና ገዳመሴታውያን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መካከል የእግር ኳስ ጫወታ ተካሂዷል።


.

Copyright © All rights reserved.