የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የ2018 ዓ.ም የ6ኛ ፣8ኛ እና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ስኬታማ ለማድረግ እየተከናወኑ በሚገኙ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እና በ1ኛ መንፈቅ የተማሪዎች ውጤት ትንተና ዙሪያ ከክፍለ ከተማ የስርአተ ትምህርት ቡድን መሪዎች እንዲሁም የፈተና ባለሙያዎችና የስራ መሪዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ አበራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የ2018 ዓ.ም የ6ኛ ፣8ኛ እና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው የዛሬው ውይይት ተግባሩ ውጤታማ እንዲሆን ክፍለ ከተሞች በስራቸው የሚገኙ ትምህርት ተቋማትን ከመደገፍ ጀምሮ በቂ የቅድመ ዝግዝጅት ስራ መስራት እንዲችሉ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን አመላክተዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም ክፍለ ከተሞች የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን የመመዝገብ ስራ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በማየት አስፈላጊውን የማስተካከያ ስራ መስራት እንደሚገባቸው ገልጸው ቢሮው በቀጣይ የ12ኛ ክፍል ፈተና በሚያስፈትኑ ተቋማት በመገኘት የመሰረተ ልማት ዝግጁ እንዲሆን እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በድጋፍና ክትትል የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
በመርሀ ግብሩ የ2018 ዓ.ም የ6ኛ ፣ 8ኛ እና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚያስፈትኑ ተቋማት መረጃና እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት በፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በለጠ ንጉሴ ከመቅረቡ ባሻገር የ1ኛ መንፈቅ የተማሪዎች ውጤት ትንተና ሪፖርት በስራ ክፍሉ ቡድን መሪ አቶ ተሾመ ደገፋ አማካይነት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።