በበይነ መረብ የሚሰጠው የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካል ከወዲሁ በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራት እንደሚገባው ተገለጸ።
(ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በከተማ አስተዳደሩ በበይነ መረብ የሚሰጠውን የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ውጤታማ ለማድረግ በተዘጋጀ የማስፈጸሚያ ስልት ዙሪያ ሂደቱን በበላይነት ከሚመሩ የኮማንድ ፖስት አባላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በከተማ አስተዳደሩ በ2017 ዓ.ም በበይነ መረብ የተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ተማሪዎች ያለምንም እንግልት ደህንነቱ የተጠበቀና ከኩረጃ ነጻ የሆነ ፈተና እንዲፈተኑ ማስቻሉን አስታውሰው በ2018 ዓ.ም የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው የሚገኙ የኮማንድ ፖስት አባላትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካል አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራ ከወዲሁ መስራት የሚጠበቅበት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኃላፊው አያይዘውም የኮማንድ ፖስት አባላቱ ፈተናው በበይነ መረብ የሚሰጥባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ አብረሆት ላይብረሪ ፣ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ፣ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች እንዲሁም በመንግስት እና በግል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ጣቢያዎች የኢንተርኔት መሰረተ ልማትን ጨምሮ በቂ ኮምፒውተሮች ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።

.