በውይይቱ የቢሮው ስትራቴጂክ ካውንስል አባላትን ጨምሮ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አመራሮች ፣ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች ፣ የቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ ኃላፊ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት እንዲሁም የክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና የአዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን የተሳተፉ ሲሆን የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በለጠ ንጉሴ የማስፈጸሚያ እቅዱን አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ክቡር ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በ2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣታቸው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ያለምንም እንከን ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ መሰጠቱን አስታውሰው ዘንድሮ የሚሰጠው ፈተና በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካል በእቅዱ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ፈጥሮ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዲችል የዛሬው መርሀግብር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ኃላፊው አያይዘውም ዘንድሮ በበይነ መረብ የሚሰጠው ፈተና በስኬት እንዲጠናቀቅ ፈተናውን የሚሰጡ የመንግስትም ሆኑ የግል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ለፈተናው ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመው ክፍለ ከተሞች ሁሉንም ባለድርሻ አካል ያካተተ የማስፈጸሚያ እቅድ በማዘጋጀት በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አወሌ መሀመድ በበኩላቸው ተቋማቸው በየደረጃው የሚገኙ መዋቅሮቹን በማስተባበር ፈተናው በሚሰጥባቸው ተቋማት በቂ የአይ ሲቲ መሰረተ ልማት እና የኢንተርኔት አገልግሎት ዝግጁ መሆኑን በድጋፍና ክትትል የሚያረጋግጥ መሆኑን አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ አበራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘንድሮ ለ50,253 ተማሪዎች ፈተናውን በበይነ መረብ ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ተፈታኝ ተማሪዎች ዋናውን ፈተና ከመውሰዳቸው በፊት የሙከራ ፈተና የሚፈተኑ መሆኑን ገልጸዋል።
.