Announcement 124 የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከላት እንዲቋቋሙና በግብዓት እንዲደራጁ ዳጋፍ ተደረገ።

124 የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከላት እንዲቋቋሙና በግብዓት እንዲደራጁ ዳጋፍ ተደረገ።

03rd April, 2026

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 124 የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከላት እንዲቋቋሙና በግብዓት እንዲደራጁ መደረጉ በድጋፍ መስጫ ማእከላቱ በተቋቋሙባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ ለመማር ማስተማር ስራዉ የሚውሉ የመረጃ መሳሪያዎችና ከልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ጋር የተያያዙ ሙያዊ ድጋፎችን በመስጠት የመማር ማስተማር ስራዉ ውጤታማ እንዲሆን ትልቅ ሚና እያበረከቱ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ለልዩ ፍላጎትና ድጋፍ መስጫ ማዕከላት ልዩ ትኩረት በመስጠት በግብዓትና በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲደራጁና አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረጉ ለመማር መስተማር ስራዉ ውጤታማነት ከፍተኛ እገዛ በማድረግ ላይ መሆኑን የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው የኮከበ ጽባህ ቅድመ አንደኛ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ት/ቤት የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ክፍል ተጠሪ የሆኑት መምህር ሄኖ ሰናይ ገልጸዋል፡፡

መምህሩ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ላይ 17 እንዲሁም በድጋፍ መስጫው ማዕከል ላይ 62 በጥቅሉ 79 የልዩ ፍላጎት ትምህርት ተማሪዎችን በ2018 የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤቱ በመማር  ላይ መሆናቸዉን ገልጸው እንደተማሪዎቹ የልዩ ፍላጎት አይነት የተሻለ ለውጥ የሚያሳዩትን ተማሪዎች በአካቶ እንዲሁም የተቀሩትን የሙያ ትምህርት እንዳገኙ በማድረግ ላይ መሆናቸዉን አብራርተዋል፡፡

አክለዉም በማእከሉ አካባቢ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከድጋፍ መስጫ ማዕከሉ ሙያዊ ድጋፍና የግብዓት እገዛ እንደሚደረግ አሳውቀው ልምድ ልውውጥም በትምህርት ቤቶች መካከል እየተደረገ የመማር ማስተማር ስራዉን ለማላቅ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አጀመ መርዞ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ 1109   ተማሪዎችን በ2018 የትምህርት ዘመን ተቀብሉ በማስተማር ላይ የሚገኝ መሆኑን እንዲሁም ለልዩ ፍላጎት ትምህርት በየጊዜው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ አክለዉም ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ውጤታማነት ከትምህርት ቢሮ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አሳውቀዋል፡፡  

.

Copyright © All rights reserved.